31/12/2024
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ በጎርጎሮሳውያን የዘመን አቆጣጠር የ2025 አዲስ ዓመትን በማስመለክት ለመላው የዓለም ሕዝብ አባታዊ መልእክት አስተላለፉ።
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን !
‹‹ወሰላም በምድር ለዕጓለ እመሕያው ሥምረቱ፤
ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ ።” ሉቃ. 2፡14
ከሁሉ በማስቀደም በመላው ዓለም ለምትገኙ፤ የጌታችን የአምላካችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን ላከበራችሁና አዲሱን ዓመት 2025 ዓ.ም. ለምትቀበሉ ልጆቻችን የመልካም ምኞታችንን ለመግለጽ እንወዳለን ።
ዘመን ከቊጥር ያለፈ ትርጉም ያለው የእግዚአብሔር ስጦታ ነው፡፡ በዘመን ውስጥ ያጣነውን እናገኛለን ፣ ያገኘነውን እንመልሳለን ። በዘመን ውስጥ ሕፃናት ሲጠነክሩ ፣ ሽማግሌዎች ይደክማሉ ። አንዱ ዘመን ላንዱ ልደት ለሌላው ሞት ሆኖ ይውላል ። እግዚአብሔር አምላካችን ከጊዜ ውጭ ቢሆንም እኛን በጊዜ ሰሌዳ ውስጥ አስቀምጦናል ። ዘመን ሳያደክመው በዘመን ውስጥ በሚለዋወጥ ማንነት እንድናልፍ ተሠርተናል ። ከጠዋት እስከ ማታ ያለው ሂደት ከልደት እስከ ሞት ያለውን ረጅም ጉዞ የሚገልጥ ነው ። በየቀኑ ዕለቱን ብቻ ሳይሆን መላው ዘመናችንን እንኖራለን ። የሰው ልጅ በዚህ ዓለም በጊዜ የተለካ በሚመጣው ዓለም ከጊዜ ውጭ የሚኖር ፍጡር ነው ። በሚሞት ሥጋ የማይሞት ነፍስን ተሸክሟል፣ በሚያልፍ ጊዜም የማያልፍ ዘለዓለማዊነትን ይጠባበቃል ። በታሪክ ውስጥ ከፍታና ዝቅታ ቢፈራረቁም ፣ ሥልጣኔዎች መጥተው ቢሄዱም ፣ አንዱ ፍልስፍና ሌላውን ቢሽረውም የዘመናት መፈራረቅ ግን ቋሚ ሕግ ሁኖ ይኖራል ። የሰው ልጆች ከመከራ ቀናት የተነሣ መኖራቸውን የሚጠሉበት ጊዜ ቢገጥምም አዲስ ዓመትን መናፈቃቸው መኖርን እንደሚፈልጉ ማሳያ ነው ። ትልቅ የምስጋና ርእስ ቢኖር እርሱም አዲስ ዘመንን ማየት ነው ። አሮጌነትን እየተውን አዲስን ዓመት የምንቀበለው ፣ ያለፈውን አሮጌ ብለን ይህን አዲስ የምንለው በማያቋርጥ ለውጥ ውስጥ መሆንን ስለምንፈልግ ነው ።
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመወለዱ የዓለምን ታሪክ ለሁለት ከፍሎታል ። ከክርስቶስ ልደት በፊትና ከክርስቶስ ልደት በኋላ እየተባለም ይጠራል ። በሃይማኖታችንም ዓመተ ፍዳና ዓመተ ምሕረት ተብሎ ለሁለት ይከፈላል ። ዓለምን ለመለወጥ ብዙዎች ወደ ዓለም መጥተዋል ። ጌታችን ግን የሰውን ሕይወት ለመለወጥ ወደ ዓለም መጥቷል ። አሁን ያለነው በጌታ ዓመት ፣ በምሕረት ዘመን ነው ። ፍርድ በሙሉነት መፈጸሙ ለዓለም ሰላም ወሳኝ ቢሆንም ምሕረት ግን እውነተኛውን የልብ ሰላም ታመጣለች ። ከእኛ ወደሚያንሱት የምናደርገው ጉዞ ፣ ራስ ወዳድነትን አሸንፈን ሌሎችን ለመርዳት የምንከፍለው መሥዋዕትነት ዓለምን የሚለውጥ ነው። ከተሞቻችን በማያቋርጥ ዕድገት ውስጥ ላያልፉ ይችላሉ ። ዕድገትም የሚቆምበት ጊዜ አለ። የሰው ልጅ የሞራል ከፍታ ግን መቆሚያ የለውምና አዲሱ ዘመን ክፉ ተግባር የሚወገድበት፤ መልካም ተግባራት የሚከናወኑበት ሊሆን ይገባዋል ።
የተወደዳችሁ የዓለም ሕዝቦች!
ያለፈው ዓመት 2024 ዓ.ም. እንደ ዓለም ብዙ ነገሮችን ብናተርፍም የከሰርንበትም ጭምር ነው ። ከተፈጥሮ አደጋዎች ይልቅ ሰው ሠራሽ በሆኑ ችግሮች ዓለምን እስር ቤት ውስጥ ቆልፈንባት ይታያል ። ሲጀመር በቀናት ውስጥ የሚያበቃ ይመስል የነበረው የራሽያና የዩክሬን ጦርነት ዓመታትን እያስቆጠረ ነው ። በመላው ዓለምም ለኑሮ ውድነትና ጫና ምክንያት ሆኗል ። ከሁሉ በላይ ሁለቱ ኦርቶዶክሳውያን ሕዝቦች የሰላም ረሀብተኛ ሆነዋል ። መካከለኛው ምሥራቅም በየዕለቱ በሚሰፋ ጦርነት ተውጦ ይታያል ። የዓለም የስበት ማዕከል በመሆኑም ብዙ ጫናዎችን እያሳደረ ይገኛል ። ስልጣኔው ይዞት የመጣው የግለኝነት ኑሮ ለብዙ የሰው ልጆች በጭንቀት ውስጥ ማለፍ ምክንያት እየሆነ ይገኛል ። መፍትሔን ከመፈለግ፣ እሳትን ከማጥፋት ይልቅ ችግሮችን የሚያባብሱ ነገሮች የዓለማችን መገለጫ ሆነዋል። ለይስሙላ የሚደረጉ የሰላም ስብሰባዎችም ተናግረን ነበር ለማለት ካልሆነ በቀር ቁርጥ ውሳኔ ያላቸው አይደሉም ።
ምድራችን ሰላምን በጣም ተርባለች ። እንስሳትና አራዊት ያለምርጫቸው በመከራ ውስጥ እያለፉ ነው ። የዓለማችን ብርቅዬ እንግዶች የሆኑት ሕፃናት እየታወኩ ነው ። ራሳቸውን መከላከል ያልቻሉ ሴቶች ልጆቻችን በፍርሃት ውስጥ አሁንም አሉ ። ይህች ዓለም አስተማሪ ቅጣት እንደሚያድናት ስታምን ብትኖርም አሁን ግን አስተማሪ ምሕረት እንደሚያስፈልጋት ግልጽ እየሆነ ይመስላል። ስለዚህ በዚህ የልደተ ክርስቶስ መታሰቢያና የ2025 ዓ.ም. መቀበያ ላይ ቆመን ይቅር መባባል፣ ለጋራ ቤታችን መሥራትና በሰዎች አለመግባባት የታወከችውን ዓለም በሰዎች ቁርጥ ውሳኔ እንድትረጋጋ የበኩላችንን ጥረት ማድረግ ይገባናል ።
በመጨረሻም አዲሱን ዓመት እየተቀበላችሁ ያላችሁ፤ አዲሱን ዓመት ከክርስቶስ ልደት ጋር አብራችሁ የምታከብሩ ወገኖቻችን ልደተ ክርስቶስ ትሕትና የተገለጠበት ነውና በትሑት ሰብእና ቆማችሁ የነደደውን እሳት እንድታጠፉ፤ ጦርነትን በሰላም ለመለወጥ የራሳችሁን ድርሻ እንድትወጡ ስንል አባታዊ የተማኅጽኖ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን ፡፡
እግዚአብሔር አምላክ መላውን ዓለም በሰላም ይጠብቅልን፤
ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ!!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!
አሜን፡፡
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ጥር 1 ቀን 2025 G.C.
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ