21/12/2014
ማዕድን ሚኒስቴር 56 የማዕድን ፍለጋ ፈቃዶችን ሰረዘ
ማዕድን ሚኒስቴር ሥራቸውን በአግባቡ አላካሄዱም ባላቸው የአገር ውስጥ የውጭ ኩባንያዎች ተይዘው የነበሩ 56 የማዕድን ፍለጋ ፈቃዶችን ሰረዘ፡፡
ሪፖርተር እንዳስነበበው ኩባንያዎቹ በወርቅ፣ በብረት፣ በከበሩ ድንጋዮችና በሌሎች ማዕድናት ፍለጋ ሥራ ለማካሄድ ከሚኒስቴሩ ፈቃድ ወስደው በገቡት ውል መሠረት ሥራቸውን ሳያካሂዱ ለረጅም ጊዜ የተቀመጡ ናቸው፡፡ ኩባንያዎቹ ፈቃዱ ሲሰጣቸው ባቀረቡት የሥራ ዕቅድ መሠረት የማዕድን ፍለጋ ሥራቸውን ሳያካሂዱ የማዕድን ፍለጋ ቦታዎችን ለዓመታት ይዘው በመቀመጣቸው ዕርምጃው መወሰዱን ምንጮች ተናግረዋል፡፡
‹‹ያለ በቂ ምክንያት የፍለጋ ቦታዎችን ያለሥራ ይዘው ለዓመታት በተቀመጡ ኩባንያዎች ላይ የማዕድን ሥራዎች ፈቃድ አስተዳደሩ ዕርምጃ ወስዷል፤›› ብለዋል ምንጮች፡፡ የሚኒስቴሩ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዕርምጃው መወሰዱን ያረጋገጠ ቢሆንም ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥቧል፡፡
ማዕድን ሚኒስቴር 272 የማዕድን ፈቃዶች የሰጠ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 209 የምርመራ ፈቃዶች ሲሆን፣ 63 የማዕድን ምርት ፈቃዶች ናቸው፡፡ በሥራ ላይ ያሉ ባለፈቃድ ኩባንያዎች ብዛት 164 ነው፡፡ የአገር ውስጥ ባለፈቃዶች 60፣ የውጭ አገር ባለፈቃዶች 68፣ እንዲሁም የጋራ ሽርክና ባለፈቃዶች 36 ናቸው፡፡
ከማዕድናት የውጭ ንግድ ከ600 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ሁለት ሦስተኛው ከባህላዊ ወርቅ አምራቾች የሚገኝ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ2024 ከማዕድን ዘርፍ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት የታቀደ ሲሆን፣ ዘርፉ ለ8,000 ዜጐች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ይገመታል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የተለያዩ ኩባንያዎች በማዕድን ሚኒስቴር የፈቃድ አሰጣጥ ሒደት ላይ ቅሬታ እያቀረቡ ነው፡፡ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ከተለያዩ አገሮች የመጡ ኩባንያዎች ሲሆኑ፣ የማዕድን ፍለጋ ፈቃድ ማመልከቻ አስገብተው ረጅም ጊዜ ቢጠብቁም ከሚኒስቴሩ ምላሽ አላገኘንም ይላሉ፡፡ አንድ የውጭ ኩባንያ ኃላፊ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ማመልከቻ ካስገቡ ሦስት ዓመት ቢሆናቸው ከማዕድን ሥራዎች ፈቃድ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ምላሽ አላገኙም፡፡ ሌሎች ኩባንያዎች በበኩላቸው ያቀረቡዋቸው ማመልከቻዎች አሳማኝ ባልሆኑ ምክንያቶች ተቀባይነት አላገኙም ብለዋል፡፡
የችግሩ መንስዔ በቅርብ የወጣው የማዕድን ምርመራ ሥራዎች የፈቃድ ጥያቄ ማመልከቻዎች የሚስተናገዱበት መመርያ ቁጥር 02/2006 ነው፡፡ የአዲሱ መመርያ ዓላማ የማዕድን ምርመራ ፈቃድ ወስደው የማይሠሩ ግለሰቦችና ኩባንያዎችን ፈቃድ እንዳያገኙ ለመከላከል የወጣ ሕግ እንደሆነ የማዕድን ሚኒስቴር ኃላፊዎች ያስረዳሉ፡፡
በአዲሱ መመርያ መሥፈርት አንድ የማዕድን ፈቃድ ጠያቂ ፈቃድ ለማግኘት ያቀረበው ማመልከቻና የቀደምት ልምዱ ታይቶ ከመቶ 75 ነጥብ ማግኘት ይገባዋል፡፡ በድርጅቱ ቀደምት ልምድ 35 ነጥብ ይሰጠዋል፡፡ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች እንደሚሉት ብዙዎቹ የኢትዮጵያን የንግድ ሕግ በመጠቀም አዲስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ኩባንያ መሥርተዋል፡፡ ‹‹በጊዜውም ለአዲስ ኩባንያ ፈቃድ አይሰጥም ያለ አካል አልነበረም፡፡ ነገር ግን በአዲሱ መመርያ መሠረት አዲስ ኩባንያ ፈቃድ አይሰጥም፡፡ በዚህና በሌሎች አሳማኝ ባልሆኑ ምክንያቶች በርካታ ኩባንያዎች ፈቃድ ተከልክለው ገንዘባቸውን ይዘው ወደ ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ለመሄድ በዝግጅት ላይ ናቸው፤›› ብለዋል ምንጮች፡፡ የማዕድን ሚኒስቴር ኃላፊዎች ይህን ክስ ያስተባብላሉ፡፡ የሚኒስቴሩ አንድ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ ለሪፖርተር እንደገለጹት ቀደም ሲል የነበረው የፈቃድ አሰጣጥ ሒደት ቀለል ያለ በመሆኑ፣ በርካታ ኩባንያዎች ለማዕድን ፍለጋ ሥራ የሚያስፈልገው እውቀትና ገንዘብ ሳይኖራቸው የማዕድን ፍለጋ ፈቃዶች በእጃቸው አስገብተዋል፡፡
‹‹አብዛኞቹ ኩባንያዎች የማዕድን ፍለጋ ቦታዎችን የሚነግዱ ደላላ ኩባንያዎች ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ፈቃድ ወስደው ምንም ዓይነት ሥራ ሳይሠሩ አሳልፈው ይሸጣሉ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ በተሰጣቸው የማዕድን ፍለጋ ቦታዎች ሥራ ሳይሠሩ መሬቱን ታቅፈው ለረጅም ጊዜ ይቀመጣሉ፡፡ ዕርምጃውን የወሰድነው ተገቢውን ጥናት ካደረግን በኋላ ነው፤›› ያሉት ኃላፊው፣ ‹‹እነዚህን ደላላ ኩባንያዎች ለመከላከል አዲስ መመርያ ማውጣት አስፈላጊ ሆኗል፡፡ የማዕድን ፍለጋ ልምድ ያለውና አስፈላጊው ካፒታል ላላቸው ኩባንያዎች አሁንም ቢሆን ፈቃድ እንሰጣለን፤›› ብለዋል ኃላፊው፡፡
የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ የማዕድን ዘርፍ ላይ በቅርቡ ባካሄደው ጥናት የማዕድን ሚኒስቴር ያሉበትን ችግሮች ነቅሶ አውጥቷል፡፡ ባለፈው ጥቅምት ወር በአዲስ አበባ ሒልተን የማዕድን ሚኒስቴር ኃላፊዎች ባሉበት ይፋ የሆነው ሪፖርት ሚኒስቴሩ የባለሙያ እጥረት እንዳለበት የገለጸ ሲሆን፣ የማዕድን ፈቃድ አሰጣጥ ሒደቱንም ተችቷል፡፡
‹‹በአሁኑ ወቅት የፍለጋ ፈቃድ ማመልከቻዎችን በመገምገም ረገድ ከፍ ያለ ክምችት ይታያል፡፡ መነሻ ላይ የነበረው ሐሳብ ግን ማመልከቻዎችን በየወሩ ለማየት ነበር፡፡ ይህ የሆነው በከፊል ማዕድን ይገኝባቸዋል ተብለው የሚታሰቡ ቦታዎችን ለመያዝ ብቻ ተብለው የሚቀርቡ ማመልከቻዎችንና ወይም አስፈላጊ እውቀትና ግብዓት የሌላቸውን ድርጅቶችን ለመግታት ታስቦ ሊሆን ይችላል፡፡ ቢሆንም ግን ማመልከቻዎችን በየጊዜው ለመገምገም ጉዳዩ የሚመለከተው የመንግሥት ተቋም ከባድ የአቅም ተግዳሮት እንዳለበት ግልጽ ነው፤›› ይላል ሪፖርቱ፡፡
የማዕድን ሚኒስቴር በ2005 ዓ.ም. ሥራ ላይ ያዋለው ኮምፒዩተራይዝድ የማዕድን ልማት ካዳስተር ሥራ መቋረጡ፣ በማዕድን ፈቃድ አሠራር ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን የዓለም ባንክ ጠቅሷል፡፡